በቀጣዮቹ 5 ዓመታት የሚተገበር የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ 5 ዓመታት የሚተገበር “የተፋሰስ አስተዳደር ድጋፍ ለጠንካራ፣ አካታችና ተስማሚ ለውጥ” የተሰኘ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡
ፕሮጀክቱ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም በውሃና መሬት ሃብት ማዕከል በጋራ የሚተገበር ሲሆን÷በዛሬው ዕለት በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ በይፋ ተጀምሯል፡፡
ከኦሞ ጊቤ ተፋሰስ በተጨማሪ በዓባይ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ተከዜ የተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንደሚተገበር የማዕከሉ ዋና ዳይሬከተር ጌቴ ዘለቀ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ እና ከአውሮፓ ህብረት የተገኘ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱ የውሃ ሃብትን በዘላቂነትና በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችሉ የቴክኒክ፣ የተቋምና የመሰረት ልማት አቅሞቸን ማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል።
በተጨማሪም የውሃ ሃብት መጠን፣ አቅርቦትና አጠቃቀምን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን መወሰንና ንዑስ ተፋሰሶችን መተግበር ያስችላል ተብሏል።
በወርቃፈራው ያለው