ስታርታፖችን ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንኩቤሽን ማዕከልን ለማስፋት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ሲከናወን የነበረው በስታርታፕ ልማት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ውድደር አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር በዚህ ወቅት÷በኢትዮጵያ አዳዲስ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የንግድ እውቀት፣ የፈጠራ ክህሎቶችና የቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ላይ በስፋት ተሰርቷል ብለዋል፡፡
ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የስታርታፕ ሚና የላቀ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ተማሪዎች የራሳቸውን የንግድ ሃሳቦች የሚያቀርቡበት የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ተዘጋጅቶ፣ ከሙያተኞች የሚሰጠው አስተያየትና ድጋፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ያግዛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ስታርታፖችን ለማፍራት መነሻ መሰረቶች መሆናቸውን ጠቁመው÷ጀማሪ ስታርታፖችን በብዛት ለማፍራት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተማሪዎች በንግድ አሰራር፣ ፋይናንስ አስተዳደር እና በቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚማሩትን ትምህርት በተግባር ላይ እንዲያውሉ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ኢኖቬሽንን ለማሳካት የግል እና የመንግስት ተቋማት ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ዩኒቨርሲቲን መሰረት ያደረጉ ስታርታፖችን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነ መጠቀሱንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡