ባለስልጣኑ የኢንቨስትመን ባንክ አገልግሎት አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንቨስትመን ባንክ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡
ሲቢኢ ካፒታል አክሲዮን ማኅበር እና ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ደግሞ የመጀመሪያዎቹ የኢንቨስትመንት ባንክ እንዲጀምሩ ፈቃድ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ኢትዮ-ፊደሊቲ ሴኩሪቲስ አክሲዮን ማኅበር – የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኝ ፣ ኤች ኤስ ቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር – የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ እና ኢኩዥን የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር – የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ሆነው ፈቃድ አግኝተዋል።
የዳበረ የካፒታል ገበያ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ብልጽግና ትልቅ መሰረት መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ አስገንዝበዋል፡፡
ዘርፉ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪው ያለበትን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያው ከአምራቾች ባሻገር መንግስት ያለበትን የበጀት ችግር ለመፍታት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወርን ሂደት ተመን ከማውጣት ጀምሮ ሕብረተሰቡም ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ በበኩላቸው፤ የእነዚህ አዳዲስ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ገበያው መምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ የአገልግሎት ብዝሃነት ያለው ጠንካራ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ለሕብረተሰቡ ከኢንቨስትመንት ባንክ እና ከማማከር አገልግሎቶች ጀምሮ እስከ የሰነደ ሙዓለንዋይ ግብይቶችን ማስፈጸምና ማከናወን ድረስ ያሉ ቁልፍ አገልግሎቶችን ለመስጠት ወሳኝ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እስከ አሁን የካፒታል ገበያው ፈቃድ ባላቸው አራት የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ብቻ ተወስኖ የነበረ መሆኑን ጠቁመው፤ ዛሬ የኢንቨስትመንት ባንክ እና የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኝ ድርጅቶችን በማካተት መስፋፋቱ የገበያው ተሳታፊዎች አዳዲስ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ አዳዲስ አገልግሎት ሰጭዎች ለገበያው ጥልቀት እና ቅልጥፍናን የሚጨምሩ ሲሆን፤ ለተሻለ የካፒታል ማሰባሰብ እና የኢንቨስትመንት እድሎችም በር ይከፍታሉ ተብሏል።
በተጨማሪም የኢንቨስተሮችን አመኔታ በማጎልበት፣ የገበያ ፍትሐዊነትን በማሳደግ እና የካፒታል ማሰባሰቢያ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ካፒታል ፈላጊ ተቋማትንም ሆነ ኢንቨስተሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በዘመን በየነ