ፌስቲቫሉ ሀገር በቀል እሴቶችን በማስተዋወቅ በቀጣናው ሀገራት አንድነትን የሚያጠናክር ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባሕል ፌስቲቫል ሀገር በቀል እሴቶችን በማስተዋወቅ በቀጣናው ሀገራት መካከል ትብብርንና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገልጸዋል።
2ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባሕል ፌስቲቫል መክፈቻ መርሐ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ የጥበባና ባህል ሚኒስትሮች፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የባህል ቡድኖች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ይህ ፌስቲቫል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ባህላዊ ምርቶችና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
ባህልና ጥበብ የሰው ልጆች አንጡራ ሀብቶች መሆናቸውን እና ድንበር አልባ በመሆኑ በሰዎች ዘንድ መስተጋብርን በመፍጠር ለትብብርና አንድነት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ማህበራዊ፣ ፖቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የባህልና ኪነ ጥበባት ቡድኖች እየተሳተፉ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን የሚያሳድጉ የኪነጥበብና የፈጠራ ሥራዎች ሀገራትን የሚያስተሳስሩና የሚያቀራርቡ ትዕይንቶች የሚቀርቡበት እንደሆነም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡