Fana: At a Speed of Life!

ብዝኃነት ለአፍሪካ መልኳም ታሪኳም ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብዝኃነት ለአፍሪካ መልኳም ታሪኳም ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደውን ሁለተኛውን የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል፣ በውቧ መዲናችንና በግዙፉ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በማስተናገዷ ታላቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።

የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር፣ በልዩ ልዩ ባህሎች ውስጥ ማደግ፣ ከተለያዩ እምነቶች ጋር መኖር – ለእኛ ለአፍሪካውያን ጌጣችን ነው ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አመልክተዋል።

ሥሪታችን ብዝኃነት ነው፤ ሕዝቦቻችን፣ ባህሎቻችንና ቋንቋዎቻችን ሰው ሠራሹን ድንበር ይሻገራሉ፤ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያም፣ የሰው ዘር መገኛና የኅብረ ባህልና የኅብረ ብሔር ማዕከል ናት ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገራችን በዚህ ዘርፍ ለቀጣናው ሀገራት ትስስር መጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክታለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም የባህል ዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ትሥሥር እንዲጎለብት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

የብዝኃ ባህል ሀብቶች እና የጋራ መገለጫ የሆኑ ዕሴቶችን ለሕዝቦች አንድነትና መግባባት፣ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም እንዲሁም ማኅበራዊ ትሥሥርን ለማጎልበት መጠቀም ይኖርብናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.