Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የእስራኤልን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ቤተ እስራኤላውያን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የዕውቀት ሽግግር መሳተፍ እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ለዚህም የኢትዮጵያና የእስራኤልን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በእስራኤል ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ቤተ እስራኤላውያን ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ÷ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማሳደግ በተለይ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቤተ እስራኤላውያን ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን ትውልድ አገር ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴት እንዲለምዱ፣ የተማሩትን እውቀት ማስተላለፍ እንዲችሉ እና በክረምት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ጎሹ በውይይቱ ወቅት÷ ኢትዮጵያውያን እና ቤተ እስራኤላውያን በትውልድ አገራቸው ሊሳተፉባቸው በሚችሉባቸው የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ሁለቱን ሀገራት በማስተሳሰር የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ከፍተኛ መሻሻል ያሳየውን የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ፣ የባህር ዳር ከተማ ሁለንተናዊ ለውጥ፣ በቀጣይ ለማከናወን የተያዙ ዕቅዶች እና በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ቤተ እስራኤላውያን መሳተፍ የሚችሉባቸውን ዘርፎች በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተሳታፊዎች በኩልም ለኢትዮጵያ ሰላምንና ልማትን እንደሚመኙ ገልጸው፤ በኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በዕውቀት ሽግግር የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

እስራኤል ያላትን የቴክኖሎጂ ልምድ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ሀብት ጋር በማስተሳሰር የሁለቱን አገራት የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻልም አስረድተዋል።

በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ መሰጠቱን በእስራኤል ከኢትዮጵያ ኢምባሲ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.