Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለአሜሪካ ኩባንያዎች በይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም ከኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና ከምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ባለው የቢዝነስ ትስስር ዙሪያ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ብናልፍ በወቅቱ፤ የንግድ ምክር ቤቱ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ትስስር እንዲጠናከር ለሚያበረክተው አስተዋጽኦ አመስግነው፣ በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ ገበያና ሀብት አንጻር የበለጠ መስራት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በተለይም አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ፖሊሲ በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የወጪ ምርቶችና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አምባሳደሩ አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱ በሚሳተፍባቸው የንግድና ኢንቨስትመንት መድረኮች ላይ ለአሜሪካ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በይበልጥ እንዲያስተዋውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አመራር በበኩላቸው በአሜሪካ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶችን በማስተዋወቅ ተጨማሪ የውጭ ገበያ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.