የትምህርት ዘርፍ በማንኛውም መለኪያ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሊሆን አይገባም – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ዘርፍ በማንኛውም መለኪያ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሊሆን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለጹ።
“የክልላችንን ሰላም በማፅናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ ሃሳብ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት የፖለቲካ፣ የሰላምና የድርጅት ሥራዎች ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ አቶ አረጋ ከበደ እንዳመለከቱት፤ የመንግስትና የድርጅት ስራዎችን ከማጠናከር ባሻገር ሰላምን የማፅናት ተግባራት በትኩረት ይከናወናሉ።
በክልሉ የትምህርት ዘርፍ በማንኛውም መለኪያ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሊሆን እንደማይገባ ጠቅሰው፤ ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱ ተማሪዎችን በቀጣይ ለመመለስ አመራሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በመድረኩ በመንግስትና በድርጅት የተያዙ የልማትና የሰላም አጀንዳዎች በውጤታማነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ሲቪል ሰርቪሱን በአመለካከት፣ በአደረጃጀትና በውጤታማነት ለመተግበር የሚያስችል የሪፎርም ማሻሻያም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደርን ጨምሮ በሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ጥራትን ባሟላ አግባብ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በክልሉ የተሻለ ሰላም መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
ልማትና የመልካም አስተዳደርን ሕዝቡ ከሚፈልገው አንፃር ብዙ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በቀጣይ ሰላምን አፅንቶ ለማስቀጠል ብሎም የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።