ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የፕሪቶሪያው ስምምነት ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘቱን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ ለሰላም ባለን ከፍተኛ ጉጉት ያሸነፍነውን ጦርነት አቁመን ለሰላም ድርድር ተቀምጠናል ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እያሸነፈ ለድርድር የተቀመጠ መንግስት እንደሌለም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ለብዙዎች ልምድ የሚሰጥ ታሪካዊ ስምምነት መሆኑን አውስተው÷ መንግስት በጦርነቱ የዜጎችን ሞት ለማስቀረት ስምምነቱን መፈረሙን አስረድተዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ውጊያ አለመደረጉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ያጣቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኙ አስችሏል ብሏል፡፡
ነገር ግን በስምምነቱ የሚጠበቁና በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ ያልተደረጉ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸው÷ለአብነትም የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በተሟላ መንገድ አለመፈጸሙን አንስተዋል፡፡
ይህ አለመሆኑ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው፤ሀገር ማልማት የሚችሉ ወጣቶች በወታደር ስም ተቀምጠው ለክልሉ የሚላከውን በጀት ለቀለብ የሚያውሉት ከሆነ ልማት ሊመጣ አይችልም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ለእነዚህ ታጣቂዎች የሚውለውን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለልማት እንዲውል ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በተሟላ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ተፈናቃዮችን በሚመለከት በራያ እና ጸለምት አካባቢዎች ጥሩ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው÷ ይሁን እንጂ በወልቃይት አካባቢ የተጀመሩ ሥራዎች በተፈለገው ደረጃ አልሄዱም ብለዋል፡፡
ሰብዓዊነትንና ፖለቲካን የመቀላቀል አካሄድ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዳይቻል እክል መፍጠሩን ያብረራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ይህን አካሄድ ማረም ከተቻለ የፌደራል መንግስት ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ጦርነት እንዳይፈጠርና ጥያቄዎች በንግግር እንዲመለሱ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት አመስግነዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሁለት ዓመት የሥራ ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ እስካሁን የነበሩ አፈጻጸሞች ተገምግመው የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሚያከብር መንገድ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በሃላፊነት መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ከህወሓትና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የጊዜያዊ አስተዳደሩን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ውይይት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መሰረት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለቀጣይ አንድ ዓመት ይቀጥላል የሚል እምነት መኖሩንና፤ በእነዚህ ጊዜያት አስተዳደሩ ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ለቀጣይ ምርጫ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ