15 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የሚሳተፉበት ሜሪ ጆይ የ5 ኪሜ ሩጫ መጋቢት 28 ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍኤምሲ) “አረጋውያንን እመግባለሁ፤ ጤንነቴን እጠብቃለሁ” በሚል መሪ ቃል የበጎ አድራጎት ገቢ ማሰባሰቢያ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር መጋቢት 28/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።
ሁነቱን አስመልክቶ አዘጋጆቹ ሜሪጆይ ኢትዮጵያ እና ብራይት ኤቨንትስ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ‹‹ሜሪ ጆይ የ5 ኪ.ሜ. የሩጫ ውድድር›› ከ12 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
የሩጫ ውድድሩ ዓላማ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሀገራችን ለሚያከናውናቸው የሰብአዊ እና የልማት ተግባራት የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ መሆኑ ተነግሯል።
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በፊት በ1986 ዓም የተመሰረተና በኢፌዲሪ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በህጋዊ መንገድ የተቋቋመ ሀገር በቀል የግብረ ሰናይና የልማት ድርጅት መሆኑ ተጠቅሷል።
ድርጅቱ እጅግ በርካታ ለሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናትና አረጋዊያን በምገባ፣ በጤና ክብካቤ፣ በትምህርትና ስልጠና በአረጋዊያን ማዕከልና በዘርፈ ብዙ የሰብአዊና የልማት ስራ ሲያከናውን መቆየቱ ተመላክቷል።
ሜሪ ጆይ አሁንም በዚሁ የሰብአዊና የልማት ስራው እንደቀጠለ የተነገረ ሲሆን ለሚደግፋቸው ሕፃናትና አረጋዊያን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማል። ከነዚህም መካከል በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚዘጋጁ ሁነቶች የሚገኘው ገቢ አንዱ ነው፡፡
በዚህ ወር መጨረሻ የሚካሔደው የሩጫ ውድድርም ለዚህ ዓላማ አካል መሆኑን የድርጅቱ መሥራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ተናግረዋል።
ድርጅታቸው አሁን ላይ እስከ 1.5 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው አሁን ላይ በአዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና እና አርባ ምንጭ ከተሞች ማህበራዊ አገልገሎቶችን የሚሰጡ ሆስፒታሎች እያስገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሆስፒታሎቹ ነፃ የህክምና አገልግሎት፣ የአረጋውያን የምገባ አገልግሎት እና እንክብካቤ፣ እንዲሁም ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ህፃናትን የገቢ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች እንዲሰማሩ የሚያስችል አገልግሎት አላቸው ብለዋል፡፡
ከሲያትል የነርሶች ማህበር እና ባለሀብቶች በተገኙ 18 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች በአዲ አበባ አስኮ እና ሀዋሳ እየተገነቡ በሚገኙት ሆስፒታሎቻቸው የኩላሊት እጥበት ማዕከላት እንደሚቋቋሙ ገልፀዋል፡፡
ድርጅታቸው ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ያገኘው የነበረው የገንዘብ ድጋፍ በመቋረጡ የሚሰጣቸው በርካታ በጎ አድራጎት ስራዎች እንደተስተጓጎሉ አንስተዋል፡፡ የሜሪ ጆይን በጎ ዓላማ በሀገራችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም አካላት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ እንዲሁም በማስተባበር አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሜሪ ጆይ የህይወት ዘመን አምባሳደሮችዩየሆኑት ታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እልፍነሽ ዓለሙ እና ፍቅሩ በቀለ መጋቢት 28 በሚካሄደው የሩጫ ውድድር በመሳተፍ ሁሉም የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡