5ኛው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራተደራዳሪ ቡድን ስብሰባ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አምሥተኛው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
በተለያዩ የድርድር ነጥቦች ዙሪያ ከ110 በላይ ጥያቄዎችን በመቀበል ውጤታማ ድርድር ያካሄደው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ማምሻውን ድርድሩን አጠናቅቋል ሲሉ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ሥድስተኛው የሥራ ቡድን ስብሰባም በያዝነው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ እንዲካሄድ ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2018 ካሜሩን ላይ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም ንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ፤ የዓለም ንግድ ቤተሰብን እንድትቀላቀል ሁላችንም የራሳችንን የቤት ሥራ ለመሥራት ተስማምተን ድርድራችንን ቋጭተናል ነው ያሉት፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናትም ቀሪ የሁለትዮሽ ድርድሮችን ጨምሮ ከጽሕፈት ቤቱ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ይኖራል ሲሉ አመላክተዋል፡፡