ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ልምድ ለጋምቢያ አካፈለች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በጋምቢያ የማዕከላዊ ባንክ ተቀዳሚ ምክትል ገዥ አብዱላዮ ሲረህ ጃሎ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ከውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት የዳበረ ልምድ እንዳላት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም፤ በአፍሪካ በትልቅነቱ ብሎም በፋይናንስ ምንጭና ከሕዝባዊ ተሳትፎ አንጻር በርካታ ተሞክሮዎች የተገኘበት ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ግድቡ በመንግሥት ቁርጠኝነትና በሕዝቦች የነቃ ተሳትፎ በራስ የፋይናንስ ዐቅም የተገነባና የሕዝቦችን አንድነት ያጠናከረ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዳይሳካ የተደረጉ ጥረቶችን በጥበብ በማለፍ፤ ግድቡ በከፊል ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር ማድረግ ተችሏል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የአፍሪካን ጉዳዮች በአፍሪካውያን በሚል መርህ የድርድር ሂደቶች የተመሩበት አግባብም ትልቅ ማስተማሪያ መሆኑን ሚኒስትሩ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡