የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የተለያዩ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል ላይ የሚሳተፉ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የደቡብ ሱዳን የባህል ሙዚየምና ብሔራዊ ቅርስ ሚኒስትር ናዲያአሮፕ ዱድ ማዮ (ዶ/ር) እንዲሁም የታንዛኒያ የማስታወቂያ፣ የባህል፣ የጥበብና ስፖርት ሚኒስትር ፓላማጋምፓ ጆን ኤዳን ምዋሉኮ (ፕ/ር) ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
በተጨማሪም የሩዋንዳ ወጣቶችና ሥነ-ጥበባት ሚኒስትር ኡቱማትዊሽማ ጄን ኔፖ አብደላህ (ዶ/ር) እና የዑጋንዳ ሥርዓተ ጾታ፣ ባህልና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አሳሞሔለን ግሬስ አዲስ አበባ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የጅቡቲ የወጣቶችና የባህል ሚኒስትር ሁቦ ሞሚን አሶወህ (ዶ/ር)፣ የሶማሊያ የባህልና መረጃ ሚኒስትር ዳኡድአዊስ ጃማን ጨምሮ የቡሩንዲ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጉዳዮች ወጣቶች ስፖርትና ባህል ሚኒስትር ገርቫይስ አምብ አባይሆ ለፌስቲቫሉ ለመሳተፍ አዲ አበባ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ተወካይ ዮላንዴኢሌቤ ማንዴምቦም አዲስ አበባ መግባታቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
እንግዶቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር ” በሚል መሪ ሐሳብ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ባህሎቻቸውን የሚያስተዋውቁበትና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መሆኑም ተመላክቷል፡፡