ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር በስልክ ለአንድ ሠዓት የዘለቀ ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገለጹ፡፡
ውይይቱ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን በሰላም ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት በሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን የቀረቡ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ትራምፕ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ሚካኤል ዋልዝ የጠራ የውይይት አጀንዳ እንዲያቀርቡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የተጀመሩ ውይይቶች እስከ አሁን በጥሩ ሁኔታ መቀጠላቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
በአቤል ንዋይ