አምባሳደር ደሚቱ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ከፍተኛ ኃላፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ረዳት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፋይናንስ ኦፕሬሽን ዲፓርትመንት ኃላፊ ሀርናን ዳነሪ አልቫራዶ ጋር ተወያዩ፡፡
በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በምታከናውነው የመስኖ ልማት እና ሌሎች ዘርፎች እያስመዘገበች ያለውን ውጤታማ ሥራ አምባሳደሯ አብራርተዋል፡፡
የድርጅቱ ድጋፍም አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጠል መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ሀርናን ዳነሪ አልቫራዶ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ውጤት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይኸውም ለአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም ሀገራት እንደተሞክሮ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማቸውም በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡