Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ የችግኞች የጽድቀት መጠን 85 በመቶ መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን 85 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም አስታወቁ፡፡

የዓለም የደን ቀን በኢትዮጵያ መከበር መጀመሩን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሁነት ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የደን ልማታችን ሕብረተሰባዊ ተጠቃሚነትን ግቡ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግኝን አልምቶ ሀገርን በሚጠቅምበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ዜጎች ከመትከል ባለፈ መንከባከብ ላይ ተሳቶፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ሥድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የተተከሉ ችግኞች ቁጥር ከ40 ቢሊየን በላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራዊ የጽድቀት መጠኑም 85 በመቶ ደርሷል ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ሠራተኞች እና አመራሮችም በምሥራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ በ70 ሔክታር ላይ የተተከለን ችግኝን ዛሬ ተንከባክበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱ እና ይህን አሃዝ በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናትም በተቋማት የተተከሉ ችግኞችን የመመልከትና የመንከባከብ ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡

በአሸብር ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.