የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ዓላማ ህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲደርሳቸው ማድረግ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲደርሳቸው ማድረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናገሩ።
ሚኒስትሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ቀርበው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ጥራት ያለው ትምህርት ማዳረስ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ሥራ ነው ብለዋል።
በተለያየ አካባቢ የሚሰጠው ትምህርት የጥራት ልዩነቱ እየሰፋ ከመጣ ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት ሰፍኗል ማለት እንደማያስችል ጠቅሰው፤ የትምህርት ጥራትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራት ችግር የቆየና ውስብስብ እንደሆነ በመግለጽ ችግሩን መፍታት ጊዜ እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ጥራት ችግሮችን በመለየት ከመምህራን ብቃት፣ ከመሰረተ ልማት እና ከትምህርት ስርዓቱ አንጻር እንዲሁም የተለያዩ ሪፎርሞችን በማድረግ የትምህርት ስርዓቱን የተሻለ ለማድረግ ብዙ ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነ አብራርተዋል።
በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ መምጣቱን አንስተው ይሄንን ለማጥበብ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሁሉም ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲኖራቸው መደረጉን የጠቀሱት ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)፤ ይህም ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ለዝግጅት ጊዜ በመስጠት ልዩነት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የመምህራንን አቅም ለማሳደግ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ አስታውሰው፤ ባለፈው የክረምት ወቅት 60 ሺህ የሚሆኑ መምህራንና 7 ሺህ ርዕሰ መምህራን ስልጠና መውሰዳቸውን በአብነት አንስተዋል።
በሚቀጥለው ክረምትም 84 ሺህ መምህራንን ለማሰልጠን መታሰቡን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከመምህራን ጥቅም ጋር በተያያዘም የመምህራንን ኑሮ ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ከክልሎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ዘርፍን ችግሮችን ለማቅለል የመምህራን ባንክ ማቋቋምን ጨምሮ የደመወዝ ጭማሪ ከመጠበቅ ባለፈ በራስ ተነሳሽነት ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበትን አማራጭ ለማስፋት እንቅስቀሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት ማጣትና ስነምግባር ለማስተካል ያለመ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው፤ ከነዚህም ውስጥ ግብረገብ በትምህርት ስርዓቱ ተካትቶ መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በእየሩስ ወርቁ