ሩሲያ በዩክሬን የኢነርጂ መሰረተ ልማት ተቋማት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም ተስማማች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሚቋጭበት ሁኔታ ላይ በስልክ ተነጋግረዋል።
በንግግራቸውም ሩሲያ ለአንድ ወር ሙሉ የተኩስ አቁም እንድታደርግ የቀረበላትን ሀሳብ አልተቀበለችም።
ነገር ግን በዩክሬን የኢነርጂ መሰረተ ልማት ተቋማት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም ከስምምነት ደርሳለች።
ፕሬዚዳንት ፑቲን እንዳረጋገጡት ሀገራቸው ሁሉን-አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የምትደርሰው ለዩክሬን የሚደረገው የውጭ ወታደራዊ ድጋፍ እና የስለላ መረጃ ማጋራት ድርጊት ሲቋረጥ ብቻ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ይህንን የሩሲያ ሀሳብ ቀደም ሲል የዩክሬን የአውሮፓ ሀገራት አጋሮች ውድቅ እንዳደረጉት ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ፤ እጅግ ጥሩ እና ውጤታማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በኢነርጂ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም ተስማምተናል፤ የተሟላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ መስራት እንዳለብንም ተግባብተናል ሲሉ ገልጸዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው አሜሪካ እና ሩሲያ የደረሱበትን የኢነርጂ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የማቆም ስምምነት ሀገራቸው እንደምትቀበለው ገልጸው፤ የስምምነቱን ዝርዝር ማወቅ እንዳለባቸው ግን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር እንደሚነጋገሩበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።