የአሮሚያ ክልል 72 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባላሃብቶች የመስሪያ ቦታ አስተላለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል የኢንቨስትመንት ቦርድ 72 ቢሊየን ብር ላስመዘገቡ ከ2 ሺህ 500 በላይ ባለሃብቶች የመስሪያ ቦታ አስተላልፏል።
ቦርዱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ÷ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሁም ግንባር ቀደም የሆኑ አርሶ አደሮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተቀባይነት ማግኘታቸውን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት 72 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 2 ሺህ 500 ባለሃብቶች የኢንቨስመንት ፍቃድ መሰጠቱን የቢሮው ሃላፊ አህመድ ኢድሪስ ገልጸዋል።
ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን÷ ኢንቨስተሮቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ሥራ እንደሚገቡ መገለጹን ከክልሉ ኢንቨስትመንት እና እንዱስትሪ ቢሮ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡