የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ዕጩ አሽከርካሪ ስልጠና በአግባቡ እንዲከናወን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳሰበ።
ባለሥልጣኑ ከአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት አመራሮችና ባለንብረቶች ጋር ብቁ አሽከርካሪ በማፍራት ሂደት በተግባር አፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ተወያይቷል።
የውይይቱ ዓላማ ብቃቱ የተረጋገጠ አሽከርካሪ ለማፍራት ከምዝገባ እና ሥልጠና እስከ ምዘና ድረስ በሚሠራው ሥራ ያሉ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ማሰልጠኛ ተቋማት ተቀራራቢ ዐቅም እንዲኖራቸው የድጋፍና ክትትል መድረክ መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን በማዘመን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የማሰልጠኛ ተቋማት ልምዳቸውን ማካፈላቸውን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
የዕጩ አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን ለማብቃት ከባለስልጣኑ ጋር በመናበብ መሥራት እንደሚገባም ተነስቷል።
አሠራራቸውን በማዘመን በክኅሎትና በሥነ-ምግባር ብቁ የሆነ አሽከርካሪ ከማፍራት አንጻር የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት ስለሚያስችል ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ተረፈን (ኢ/ር) ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ውይይቱን መርተውታል ፡፡