የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ ዐዋጅ ለቋሚ ኮሚቴው ተመራ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ ዐዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ረቂቅ ዐዋጁን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ ወቅትና ድኅረ አደጋ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የፌደራልና የክልል አሥተዳደር ተቋማትን የውስጥ ዐቅም ለመገንባት የሚያስችል ነው ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
ቅጽበታዊ አደጋ ሲከሰትና ከዐቅም በላይ ሲሆን፤ የአስቸኳይ ጊዜ እወጃ ሥርዓት ለመዘርጋት ብሎም የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የዘላቂ ልማት እና የሰላም ግንባታ ዕቅዶችን ለማስተሳሰር የሚያስችል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡
ረቂቅ ዐዋጁ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት መቋቋምን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣ የኮሚሽኑን ተግባርና ኃላፊነትን ጨምሮ ሌሎች ድንጋጌዎች ማካተቱም ተብራርቷል፡፡
ረቂቅ ዐዋጁ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 16/2017 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ተመርቷል።