Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 11 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለ2017/18 የምርት ዘመን 11 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ የክልሉ ህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ኃላፊ ጀማል ከድር የምርት ዘመኑን የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በበጀት አመቱ 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ዓመት የተሸጋገረውን 900 ሺህ ኩንታል ጨምሮ ለምርት ዘመኑ በአጠቃላይ 11 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ መሆኑን አብራርተዋል።

በምርት ዘመኑ የሚቀርበው ማዳበሪያ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

እስካሁን 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን ጠቅሰው፤ 310 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

ዩሪያ እና ዳፕ የተሰኙት የአፈር ማዳበሪያ አይነቶች እየቀረቡ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ የክልሉ መንግስት ከ32 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ለማዳበሪያ ግዢ ድጎማ አድርጓል ብለዋል።

በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት በዲጅታል የታገዘ መሆኑን አንስተው፤ ስርጭቱ በህብረት ስራ ዩኒየኖች በኩል የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።

የኔትዎርክ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ክፍያውን በባንክ በኩል መፈጸም ይችላልም ብለዋል፡፡

በስንታየሁ አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.