Fana: At a Speed of Life!

በህዝብና በጭነት አገልግሎት የተሰማሩ አሽከርካሪዎችን ብቃት ለመለካት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል በህዝብና በጭነት አገልግሎት የተሰማሩ አሽከርካሪዎችን ብቃት ለመለካት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የአሽከርካሪዎችን ብቃት ለመመዘን ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመከላከል እንዲቻል በህዝብና በጭነት አገልግሎት የተሰማሩ የንግድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎችን ብቃት መለካት የሚያስችል ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

የብቃት ምዘናው በየደረጃው ተከፋፍሎ የሚሰጥ እንደሆነ እና በመጀመሪያ ዙር የሀገር አቋራጭ አውቶቡሶችንና የድንበር ተሻገሪ የጭነት ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎችን ብቃት መለካት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል።

አሽከርካሪዎች ባሉበት ቦታ ለብቃት ምዘናው እንዴት መመዝገብ እና እንዴት የተሃድሶ ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ሲስተሙን ካበለፀገው ኤስዲኤስ ከሚባለው ተቋም ጋር ውይይት መደረጉም ተጠቁሟል።

ከሰነዶች ዝግጅት ባሻገር አሰራሩን ተፈፃሚ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቀጣይ ውይይቶች እንደሚደረግ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.