የባህር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የጣናን ውበት ይበልጥ የሚገልጥ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባህር ዳር ከተማ ጣናን መሰረት አድርጎ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የጣናን ውበት ይበልጥ የሚገልጥ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱ ነዋሪዎች ከነፋሻማው የጣና ውብ ተፈጥሮ ጋር በምቹ ጎዳናዎች እንዲገናኙ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
ከኮሪደር ልማት በተጨማሪም ባህር ዳር የምትታወቅባቸውን የዘንባባ ዛፎች መልሶ ማልማት ሌላው ተጠቃሽ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ2029ን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን አስታውሰው፤ 52 ሺህ ተመልካቾችን እንዲይዝ ተደርጎ እየተገነባ የሚገኘው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዚህ ቀደም የታዩበት ችግሮችን በማሻሻል ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መልኩ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የስታዲየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከእግር ኳስ ጨዋታ ሜዳነት ባሻገር የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንዲሆን በማሰብ እየተሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ባህርዳር በዙሪያዋ እንደ ጎርጎራ ያሉ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች የተገነቡ መሆናቸው ከተማዋ ለቱሪስቶች መሸጋገሪያ የምትሆንበት ዕድልን የፈጠረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡