የአፋርና ሶማሌ ሕዝብን ወንድማማችነትና ትብብር ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል- አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋርና ሶማሌ ሕዝብን ወንድማማችነትና ትብብር ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ፡፡
የአፋር እና ሶማሌ ወንድም ሕዝብ የጋራ ኢፍጣር መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተካሂዷል፡፡
አቶ አወል አርባ በዚህ ወቅት÷ በጋራ ኢፍጣር መርሐ ግብሩ ለታደሙ እንግዶች የእንኳን ደሕና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የአፋርና ሶማሌ ክልሎችን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ ወንድማማችነት፣ የልማት ተጠቃሚነት እና አብሮነት ለማጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡
ቀደም ሲል በሰው ሰራሽ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስቆም ዛሬ ሃላፊነቱ በእኛ ላይ ወድቋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአፋርና ሶማሌ ሕዝብን ወንድማማች እና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርም የየክልሎቹ አመራሮች አርአያ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው÷የሶማሌ እና አፋር ክልሎች በለውጡ መንግስት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘታቸውን አውስተዋል፡፡
ለአብነትም ከለውጡ በፊት ክልሎቹ ከልማትና ሌሎች ጉዳዮች ተገልለው እንደነበር ጠቅሰው÷አሁን ላይ ሁለቱ ክልሎች በፖለቲካው ዋና ተዋናይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም በለውጡ የተገኘውን መሻሻል በመጠቀም ከግጭት ይልቅ አብሮነትን በማጠናከር ወደ ልማት እና ብልጽግና መጓዝ ይገባል ብለዋል፡፡
በአፋር ሰመራ ለተደረገላቸው አቀባበል እና ለጋራ ኢፍጣር መርሐ ግብሩ መስተንግዶም ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪሰ÷ሁለቱ ክልሎች ተቀራርበው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በርካታ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመው÷ይህን ትስስር ለማጠናከርና ወንድማማችነትን ለማጉላት የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እሰልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ÷በተያዘው ረመዳን ወር በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እየተጉ ያሉ አካላትን አመስግነዋል።