የዓለም ንብ ቀንንና የምግብ ሥርዓት ሽግግር ዓውደ ጥናትን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም የንብ ቀንን እና የዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ዓውደ ጥናትን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ ከዓለም እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ረዳት ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ቀጣና ተወካይ አበበ ሃይለገብርኤል (ዶ/ር) እና በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይዚ ሙድዚን ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያ ዘንድሮ የምታስተናግደው 2ኛው የዓለም ንብ ቀንን እና ዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ዓውደ ጥናት እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉ ኢኒሼቲቮች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷የዓለም ንብ ቀንን እና ዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ዓውደ ጥናትን ለማካሄድ ኮሚቴ ተዋቅሮ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዓለም ንብ ቀን ዘንድሮ ከፊታችን ግንቦት 12 እስከ 14 ቀን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ዓውደ ጥናት ሐምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳሉ፡፡
በሁለቱ ዝግጅቶች እና የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉ ኢኒሼቲቮች ጋር በተያያዘ በቀጣይ በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡