አቶ አሕመድ ሺዴ ከዩኒሴፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኪቲ ቫን ደር ሃይጅደን ጋር በትብብር በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ተወያዩ፡፡
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡባካር ካምፖም መገኘታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡
በምክክራቸውም ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት እና አጋርነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ሕጻናት በሁሉም ቦታ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማስቻል ኢንቨስት በሚደረግባቸው መስኮች ላይ መምከራቸው ተጠቅሷል፡፡