Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የተከሰተውን የዳልጋ ከብቶች በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተውን የዳልጋ ከብቶች በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት እንዳለው የሚገመት በሽታ የዳልጋ ከብቶችን እያጠቃቸው እንደሆነ ተነግሯል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ጤናና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ ኢዮብ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በሽታው በክልሉ ጋሞ፣ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ላይ ተከስቷል።

የበሽታው ምልክት ከመጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መታየቱን ገልጸው÷ የበሽታውን ምንነት ለማጣራትና ተገቢውን ህክምና ለመስጠት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሟል ብለዋል።

ቡድኑ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢ ላይ በመገኘት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሽታው እንዳይዛመት የበሽታው ምልክት የታየባቸውን የዳልጋ ከብቶች በመለየት ክትትልና ህክምና እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምልክቱ ያልታየባቸው ከብቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

በበሽታው የሞቱ ከብቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር አዲሱ÷ መረጃዎችን የማጣራት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ዝናብ በሚገባበትና በሚወጣበት ወቅት ከብቶች ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች መኖራቸውን አንስተው÷ በእንስሳቶች ላይ የተለያዩ ምልክቶች መታየቱንም ተናግረዋል።

ለእንስሳቱ ክትባት ለመስጠት የሚያስችል ዓቅም በመኖሩ ኅብረተሰቡ እንስሳቶችን እንዲያስከትብ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.