የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያውን የቢዝነስ ጀት አውሮፕላን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተረከበው ቦይንግ 737-800 የተሰኘ የቢዝነስ ጀት አውሮፕላን ልዩ አገልግሎት ለሚሹ ደንበኞቹ እንደሚውል ተጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም ለልዩ በረራዎች የሚውሉ አገልግሎቶችን በመደበኛ አውሮፕላኖች ሲሰጥ መቆየቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
አዲሱ አውሮፕላን ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ውስጣዊ ክፍሎች እንዳሉት ገልጸው፤ በመደበኛ አገልግሎት ላይ ይፈጥር የነበረውን ጫና እንደሚቀንስ ጠቁመዋል።
አየር መንገዱ በቻርተር አውሮፕላን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አቅሙን ለማሳደግ መሰል አውሮፕላኖች እንደሚያግዙት ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በ2035 የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት የያዘውን ውጥን ለማሳካት መሰል ተጨማሪ የቢዝነስ አውሮፕላኖችን ወደ ስራ እንደሚስገባ ተገልጿል።
በሚኪያስ ዓለሙ