ለልማት ሥራ በሕጉ መሠረት መሬት ለጠየቁ አካላት እንዲሰጣቸው ተወሰነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ አሥተዳደር የልማት ሥራ ለማከናወን በሕግና መመሪያ መሠረት መሬት ለጠየቁ አካላት ተዘጋጅቶ የተቀመጠው መሬት እንዲሰጣቸው ውሳኔ ተላለፈ፡፡
የአሥተዳደሩ ካቢኔ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ መሬትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት፤ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል የክትትል ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በተጨማሪም በአሥተዳደሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በሕግና በመመሪያ መሠረት የመሬት ጥያቄ ላቀረቡ አልሚዎች ተዘጋጅቶ የተቀመጠው መሬት እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡
እንዲሁም ካቢኔው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን የድሬዳዋ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡