Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶችን እየዘረጋች ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አህጉራዊ የፋይናንስና ምጣኔ ሃብት የሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት፥ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የአፍሪካን ድንበር የለሽ ነፃ የሸቀጥና የአገልግሎት ግብይት መሻት ተስፋን እውን ለማድረግ ከምኞት የዘለለ ሥራ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ለረጅም ጊዜያት የአፍሪካ የንግድ ሥርዓት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ተጨባጭ ርምጃና ስትራቴጂካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ሀገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ከማጽደቅ ባለፈ ወደ ተግባር መለወጥና ስኬታማ ብሔራዊ የትብብር ኮሚቴ አዋቅሮ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ እሴት የተጨመረበት ምርታማነት፣ የፓን አፍሪካ ምርምር ዕድገት፣ ግልጽና ተገማች የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ዕድገት፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎና አህጉራዊ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት አቅም ማጎልበት ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያ የንግድ ውህደት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአብነትም የኢትዮ-ጅቡቲን የሚያስተሳስር የምድር ባቡር መስመር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምና የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ምሳሌ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኛትን የድንበር ተሻጋሪ ኮሪደር፣ የንግድና ትራንስፖርት መንገድ መሰረተ ልማት ግንባታም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.