የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት – የባሕር ዳር ልምድ
ዛሬ የባሕርዳርን ከተማ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ተመልክቻለሁ። ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ተዋሕደው ባሕርዳርን ይበልጥ ውበቷን እያወጡት ነው። ከተማዋን የንግድና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ አመራሩ ከሚያደርገው ጥረት የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
1. ባሕር ዳር በፈተና ውስጥ የመጽናት ምሳሌ ናት፤ ባለፉት ዓመታት የነበረው ፈተና እያለፈ ነው። ባሕር ዳር በፈተናው ውስጥ ሥራዋን አላቋረጠችም። እንዲያውም ለፈተና የተወረወረውን ድንጋይ ለግንባታ ተጠቅማበታለች።
2. የጣና መከፈት የማስተሣሠር(ኮኔክቲቪቲ) መርሐችን መገለጫ ነው። የልማት ሥራዎቻችን መመጋገብ እና መተሣሠር እንዳለባቸው የባሕር ዳር ኮሪደር ምሳሌ ይሆናል። ለብዙ ዘመናት ከከተማው ተለያይቶ የነበረው ጣና ወደ ስምንት በሚደርሱ ቦታዎች ከኮሪደሩ ጋር ተገናኝቷል። ይሄም ከመዝናኛነቱ ባሻገር ከተማዋን ነፋሻማ አድርጓታል።
3. ነባር ዕሴት ላይ አዲስ ዕሴት መጨመር። በመደመር መንገድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በነባር ዕሴቶቻችን ላይ አዳዲስ ዕሴቶችን ጨምረን መገንባት አለብን። ባሕርዳር የጣና ሐይቅና የዓባይ ወንዝ መገናኛ ናት።
ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የዘንባባ ዛፎች አሏት። በዚህ ላይ የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ ውበት ሰጥቷታል።
4. የአካባቢ ተቋማት ፈጠራ እየጨመሩ ልማትን እንዲያሣልጡ ማድረ፤ በባሕር ዳር ኮሪደር የለበሱት ንጣፎች እና የቆሙት መብራቶች በአካባቢው ተቋማትና ባለሞያዎች የተዘጋጁ ናቸው። በቀጣይም አካባቢያዊ ክሂሎትንና ዐቅምን መጠቀም የበለጠ መለመድ አለበት።
5. ባሕርዳርን የስፖርትና የቅርስ ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ፦ በጣና ዙሪያ ያሉት ታሪካዊ ሥፍራዎች፤ ከጣናና ከዓባይ ጋር ተያይዘው የተሠሩት ወደቦችና መናፈሻዎች፤ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የዓባይ ዘመናዊ ድልድይ እና ሌሎቹም ልማቶች ባሕር ዳርን የ22ኛው መክዘ የንግድና ቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት ነው።
6. የአመራር አርአያነት፦ አመራር ሠርቶ የሚያሠራ ፣ ቀድሞ የሚያስከትል መሆን አለበት። የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የራሳቸውን ጽቤት አካባቢ አስተካክለው ኮሪደሩን በመሥራት አርአያ መሆናቸው ትምህርት የሚሆን ነው።
ባሕርዳር ከዚህም በላይ መሥራት የምትችል ናት። ይሄ መጀመሪያዋ እንጂ የመጨረሻዋ አይደለም። ጽዳቱን ባህል ማድረግ፤ የተሠሩ አካባቢዎችን ጥንቅቅ ማድረግ፤ ተቋማት አካባቢያቸውን እንዲቀይሩ ማትጋት፤ ንግድን፣ ቱሪዝምን ና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ማበረታታት፣ ከሕዝቡም ከአመራሩም ይጠበቃል።