Fana: At a Speed of Life!

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያዘጋጁልን ኢፍጣር ኢትዮጵያ ለስደተኞች ያላትን ክብር ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያዘጋጁልን የኢፍጣር መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ለስደተኞች ያላትን ክብር በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች በብሔራዊ ቤተመንግስት የኢፍጣር መርሃ ግብር አከናውነዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ኢትዮጵያ በችግራችን ወቅት የደረሰችልን ባለውለታችን ናት ብለዋል።

የኢፍጣር መርሃ ግብሩም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ያላትን እንክብካቤ የሚያሳይ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከየመን የመጣችው ኢትሳም ካሊድ፤ በኢፍጣር መርሃ ግብሩ ላይ ስትሳተፍ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ ተናግራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዘጋጁልን የኢፍጣር መርሃ ግብር ከቤተሶቦቻችን ጋር ያለን ያህል እንዲሰማን አድርጎናል ነው ያለችው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለስደተኞች እያደረጉት ላለው እንክብካቤም ምስጋና አቅርባለች።

ከኢራቅ እንደመጣች የተናገረችው ኢስማህ ኢሳም በበኩሏ ከሀገራችን ችግር ገጥሞን ወደ ኢትዮጵያ መጥተን መኖር ከጀመርን ወዲህ ጥሩ አቀባበል ተደርጎልናል ብላለች።

በብሔራዊ ቤተመንግስት የተዘጋጀው የኢፍጣር መርሃ ግብርም አብሮነት በተግባር የታየበት መሆኑን ጠቅሳ፤ ይህም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ያላትን ክብር እንደሚያሳይ ተናግራለች።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፍጣር መርሃ ግብር ስላዘጋጁልን የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮልናል ስትልም ነው የተናገረችው።

ከሶሪያ የመጣው ጀሚል በሰም፤ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይና ለስደተኞች ክብር ያላቸው ደግ ህዝቦች ናቸው ብሏል።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ስደተኞች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገች መሆኑን የተናገረችው ደግሞ ከሱዳን የመጣችው ነጃት ሁሴን ናት።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስደተኞችን ተቀብላ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ ተጠቃሽ ሆናለች ነው ያሉት።

በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የኢፍጣር መርሃ ግብር ከ12 ሀገራት የመጡ ስደተኞች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በየዓመቱ ይህን በጎ ተግባር ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.