ክልሉ የይርጋጨፌ ቡናን ለቻይና ገበያ ለማቅረብ እየሠራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥራት ያለው የይርጋጨፌ ቡናን ለቻይና ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በተገኙበት የክልሉ የቡና ጥራትና ግብይት ቁጥጥር አስተግባሪ ግብረ ኃይል የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የቡና ጥራት አጠባበቅና አቅርቦት ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለግብርና ትኩረት በመሥጠት ቡና እና ቅመማቅመምን ማምረት እና ወደ ውጪ መላክ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሠራ መሆኑን ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ይርጋጨፌ፣ አማሮ እና ሌሎች ጥራት ያላቸው ቡናዎች በክልሉ እንደሚመረቱ ጠቅሰው፤ ዘርፉ የውጪ ምንዛሪ በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
የቡና ማሳን በማስፋት በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራት ይገባል ማለታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ተዓማኒ እና ጥራት ያለው ቡና በደቡብ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እንዲመረት ግብረ ኃይሉ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በኢትዮ ቻይና የልማት ትብብር በተፈጠረ የንግድ ትስስር መሠረትም፤ ጥራት ያለው የይርጋጨፌ ቡና ወደ ቻይና ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ተሞክሮም ወደ ሌሎች ቡና አምራች አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡