አሜሪካ በሁቲ አማጺያን ይዞታዎች የአየር ጥቃት ፈፀመች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በየመን የሁቲ አማፂያን ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈፀሟን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ገለፁ፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ የሁቲ አማጺያን በአሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ ሚሳይሎችን በመተኮስ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ እና የአጋሮቿ መርከቦች ላይ ላይ ጥቃት መፈፀሙን አብራርተዋል፡፡
የአማጺ ቡድኑን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማስቀረት የአየር ጥቃቱ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ለአሜሪካ ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጸው ቡድኑ፤ በአየር ጥቃቱ በጥቃቱ ቢያንስ 31 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 101 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጿል።
አማጺ ቡድኑ በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ ውስጥ ባሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት አሜሪካ እና በጥቃቱ ተሳትፎ የሌላትን እንግሊዝን መውቀሱን ቢቢሲ ዘግቧል።
በፈረንጆቹ 2023 ከህዳር ወር ጀምሮ ቡድኑ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚሳኤል፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በአነስተኛ ጀልባዎች በመታገዝ በደርዘን የሚቆጠሩ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወቃል።
የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ መርከብ በአካባቢው በሰላም ከተጓዘ ከአንድ አመት በላይ ማስቆጠሩን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ገልጸዋል።