በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ29ኛ ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር አርሰናል በሜዳው 10 ሠዓት ከ30 ላይ ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
በ55 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል፤ ቼልሲን ለማሸነፍ እና ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ወደ ሜዳ ይገባል።
በሁሉም ውድድር ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ቼልሲ በበኩሉ፤ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እና በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ይፋለማል።
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው ባለ ሜዳው ቡድን አርሰናል፤ በሁሉም ውድድር ባደረጋቸው ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ሁለቱ የለንደን ክለቦች በቅርቡ ካደረጓቸው አምስት የእርስ በርስ ግንኙነቶች አርሰናል በሦስቱ ሲያሸንፍ፤ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በተመሳሳይ ቀን 10 ሠዓት ከ30 ላይ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሀም ሆትስፐር ወደ ክራቨን ኮቴጅ አቅንቶ ፉልሀምን ይገጥማል።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ሌስተር ሲቲ በሜዳው ኪንግ ፓወር ማንቼስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በ34 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ሌስተር ሲቲ ደግሞ በ17 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሣምንቱ አጋማሽ በዩሮፓ ሊግ ድል የቀናው ማንቼስተር ዩናይትድ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እና ነጥቡን ከፍ ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሁሉም ውድድር ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳነው እና ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኘው ሌስተር ሲቲ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ