በጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ከ3 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ተመረተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት በጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ከ3 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት መቻሉ ተገለጸ።
በቀን በአማካይ ከ500 ኪሎ ግራም በላይ የዓሣ ምርት እየተመረተ መሆኑን በዳውሮ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ጮራሞ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በዞን ደረጃ 4 ሺህ 200 ቶን ዓሣ ለማምረት መታቀዱን የገለጹት ኃላፊው÷ በስምንት ወራት ውስጥ 3 ሺህ 107 ቶን ዓሣ ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል።
የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በተፈጠረው የሰው ሰራሽ ሐይቅ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው 160 ወጣቶች በተለያዩ ማኀበር ተደረጅተው ዓሣ እያመረቱ መሆናቸውን ገልጸው÷ በሐይቁም በርካታ የዓሣ ዝርያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ የሚያመርቷቸውን ዓሣዎች ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ 1 ኪሎ ግራም በአማካይ ከ200 እስከ 300 ብር እየሸጡ ናቸው ያሉት አቶ አስፋው÷ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙና ወደ ሌሎች ከተሞችም ወስደው መሸጥ እንዲችሉ የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ጋር በተያያዘ በዓሣ ምርት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ቀጣይ ሌሎች ወጣቶችም በዘርፉ ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአድማሱ አራጋው