Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ ምክር ቤት የአንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት አነሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የአንድን የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው አቶ ዮሐንስ ተሰማ የተባሉ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ተገልጿል።

የምክር ቤት አባሉ ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣ የክልሉንና የምክር ቤቱን ክብር የሚነኩ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ማሰራጨታቸው ተገልጿል።

በተለይም የክልሉ ምክር ቤት 6 ዙር 5ኛ ዓመት 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ውሳኔዎችን ካሳለፈ በኋላ በዚህ ድርጊት መሳተፋቸውን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ሃሚድ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ጠቅሰዋል፡፡

እኚሁ የምክር ቤት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያነሳሳ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሠራጨታቸውና፣ መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አመላካች መረጃዎች መኖራቸውም ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባል በተጠረጠሩበት ጉዳይ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት የአቶ ዮሐንስ ተሰማ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.