ኢትዮጵያ የቻይና ገበያን ለመጠቀም እየሠራች መሆኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የቻይና ገበያን ለመጠቀም እየሠራች መሆኗን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱበት 55ኛ ዓመት “55 ዓመታት ጠንካራ አጋርነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከብሯል፡፡
አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ በትብብር እየሠራን ነው ሲሉ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቻይና ገበያን ለመጠቀም እየሠራች ነው፤ በጥራት በማምረትና በመሸጥ ተወዳዳሪ እንሆናለን፤ ለዚህ ደግሞ ቻይና ያዘጋጀችውን የዜሮ ታሪፍ መጠቀም እንችላለን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም፤ በመተማመን፣ በመከባበር እና በመተባበር ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሀገራቱ የንግድ ልውውጥ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ የጥራጥሬ ምርቶችን ለውጪ ገበያ እያቀረብን ነው፤ በቀጣይም የካሳቫ እና እንስሳት ምርቶችን ወደ ቻይና ለመላክ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመሠረተ-ልማት ዘርፍ ጠንክራ እየሠራች መሆኗን ያነሱት አምባሳደሩ፤ ቻይና በዘርፉ እድትሰማራ ፍላጎት አለን ብለዋል፡፡
በዳዊት መስፍን