አምባሳደሮች የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጎብኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዚህ ጉብኝት ላይ፤ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ይቭጌኒ ተረኪንን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር እና የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ቡድን መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በግድቡ ወቅታዊና የግንባታ ሂደት ላይ ለጎብኝዎቹ ገለፃ ማድረጋቸውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በገለጻቸውም በግድቡ ግራ እና ቀኝ ሁለት የኃይል ማመንጫ ክፍሎች፣ በግድቡ በግራ በኩል ሥድስት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እንዲሁም በግድቡ ቀኝ በኩል ሰባት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
ውኃው ከላይ ተንደርድሮ ተርባይኑን በኃይል በመምታት ኃይል ካመነጨ በኋላ፤ በተርባይኑ ሥር ወደ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ ከግድቡ 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሠዓት በዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ማስገባት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡