Fana: At a Speed of Life!

ትግራይ ክልል ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ጦርነት እንዳይገባ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል – አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትግራይ ክልልን ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ጦርነት ለመክተት የሚሞክረው በክልሉ የሕግ ተቀባይነት ያጣው የሕወሓት አንጃ ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ወቅታው ሁኔታ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ትግራይ ክልልን ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ጦርነት ለመክተት የሚሞክረው በክልሉ የሕግ ተቀባይነት ያጣው የሕወሓት አንጃ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው ይህ አንጃ ጉባዔ አድርጌያለው በሚል ሰብብ የተወሰኑ በጥቅም የተሳሰሩ የጸጥታ ሀይሉ ሀላፊዎችን በመያዝ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንጃው በቀበሌ፣ ወረዳ እና ዞን የተቋማትን ማሕተም በሕገ ወጥ መንገድ እየነጠቀ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ያቀረበው ይፋዊ ጥያቄ አለመኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

ትግራይ ክልል ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ነው ፍላጎቴ ያሉት አቶ ጌታቸው÷ ለዚህም የፌዴራል መንግስት የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአስማማኝ ሁኔታ በሁሉም ወገን እንዲተገበር እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የፌደራል መንግስቱ ክልሉ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ በአሰራሩ መሰረት ጣልቃ መግባት እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡

አሁንም በትግራይ ክልል በርካታ ሰራዊት መኖሩን ጠቀመው÷ ይሁን እንጂ ችግር እየፈጠሩ ያሉት በክልሉ የህግ ተቀባይነት ያጣው የሕወሓት አንጃ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ የተወሰኑ የጸጥታ ሀይሉ ሀላፊዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ትግራይ ክልልን ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ጦርነት ለመክተት የሚሞክረው የሕወት አንጃ ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ድርጊቱን ለማስቆም የክልሉ ሕዝብ፣ የፌዴራል መንግስትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የበኩላቸውንሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.