የሕብረቱ ኮሚሽን አዲሱ ሊቀመንበር ስልጣናቸውን በይፋ ተረከቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ተመራጩ ሊቀመንበርን ማህሙድ አሊ የሱፍን ጨምሮ ከተሰናባች የኮሚሽኑ አመራሮች ዛሬ ይፋዊ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።
በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የተደረገው የርክክብ ስነ ሥርዓቱ የአንጎላ ፕሬዚዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ጆአዎ ሎሬንሶ፣ ተሰናባች እና አዲስ የሕብረቱ ኮሚሽን አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የካቲት 9 እና 10 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የጅቡቲው ማህሙድ አሊ የሱፍ አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና አልጄሪያዊቷን አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲን የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመበር አድርጎ መምረጡ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ማህሙድ አሊ የሱፍ ከሙሳ ፋቂ ማህማት፣ አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ከሞኒክ ንሳንዛባግዋ (ዶ/ር) ስልጣናቸውን መረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም ጉባዔው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብስባ የመረጣቸውን ኮሚሽነሮች ውጤት ማጽደቁ ይታወቃል።
የሌሴቶው ሞሰስ ቪላካቲ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሌራቶ ማታቦጅ የኮሚሽኑ የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽነር እና ጋናዊቷ አምባሳደር አማ ቱም-አሞሃ የኮሚሽኑ የጤና፣ የሰብዓዊ እና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር ሆነው ተመርጠዋል።
ጋናዊው አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽነር ሆነው በድጋሚ መመረጣቸው ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት ሞሰስ ቪላካቲ ከአምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፣ ሌራቶ ማታቦጅ ከአማኒ አቡ-ዘይድ (ዶ/ር) እና አምባሳደር አማ ቱም-አሞሃ ከአምባሳር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ ጋር አዲሱ ቦታቸውን ተረክበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አዲስ ተመራጭ ከፍተኛ አመራሮች ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።
ተመራጮቹ በተመደቡበት ቦታ ለቀጣይ አራት ዓመታት ኮሚሽኑን ያገለግላሉ።