በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚከናወነው የላሊበላ-ኩልመስክ-ሙጃ መንገድ ግንባታ…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 48 ነጥብ 78 ኪሎሜትር የሚረዝመው የላሊበላ – ኩልመስክ – ሙጃ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ሒደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የዲዛይን ፣ የአፈር ጠረጋ ፣ የቆረጣ ፣ የሙሌት ፣ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ የሰብ ቤዝ ሥራዎች እንዲሁም የድልድይ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ግንባታውን ዓለም አቀፉ ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪነግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እያከናወነ ሲሆን ÷ የማማከሩንና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ቤዛ ኢንጅነሪንግ ኬኒያ ሊሚትድ እያከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የመንገዱ አጠቃላይ የጎን ስፋት በገጠር ከ8 እስከ 10 ሜትር ፣ በቀበሌ 16 ሜትር እንዲሁም በወረዳ 20 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
የግንባታ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን÷ለዚህም 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መያዙ ነው የተገለጸው፡፡
የግንባታ ግብዓቶችንና ማሽሪዎችን ለማማጓጓዝ በአካባቢው የሚስተዋለው የጸጥታ ችግርና በመንገዱ ክልል ውስጥ የተካተቱ ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት በግንባታ ሒደቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው መቆየታቸው ተጠቁሟል፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ ከአካባቢው አስተዳደር እና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በመድረጉ አሁን ላይ የተሻለ የፕሮጀክት አፈፃፀም የተመዘገበ ሲሆን÷ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
መንገዱ ሲጠናቀቅ የላሊበላ፣ ኩልመስክ እና ሙጃ ከተሞችን በቅርበት እንደሚያስተሳስርና ወደ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት መዳረሻ በመሆን ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚያስችልም የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢው የሚመረቱትን የዘንጋዳ ፣ የገብስ እና ባቄላ ውጤቶች ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ እንደሚያፋጥን ይጠበቃል።