Fana: At a Speed of Life!

በ500 ሚሊየን ብር ካፒታል ሥራ የጀመረው ፓሮን ትሬዲንግ የሙከራ ምርት ማምረት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በ500 ሚሊየን ብር ካፒታል ከበቆሎ ምርት ስታርች ለማምረት ሥራ የጀመረው ፓሮን ትሬዲንግ የማሽን ተከላ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የሙከራ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡

የባህር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስኪያጅ ጥሩየ ቁሜ ኩባንያው 2 ሄክታር መሬት ተረክቦ የግንባታ እና የማሽን ተከላ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ኩባንያው ከ4 ሺህ በላይ ከሚሆኑ አርሶ አደሮች ጋር ዘላቂ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዲኖረው የሚያስችል የገበያ ትስስር መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

ምርቱን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ የተገለጸው የፓሮን ትሬዲንግ ኩባንያ፣ 592 ሺህ ኩንታል በቆሎን በግብዓትነት እንደሚጠቀም አስረድተዋል፡፡

ይህም ለአካባቢው በቆሎ አምራች አርሶ አደሮች ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር ከመፍጠር በተጨማሪ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኩባንያው አሁን ላይ ለ300 የአካባቢው ወጣቶች ዘላቂ የሆነ የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን÷ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.