በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚደረገውን የጸረ-ሰላም ሃይሎች አካሄድ በአግባቡ መገንዘብ ይገባል – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚደረገውን የጸረ-ሰላም ሃይሎች አካሄድ በአግባቡ መገንዘብ እንደሚገባ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን ህዝቡን በግጭት አዙሪት ውስጥ በመጥመድና የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር የቡድን ፍላጎታቸውን በህዝብ ላይ ለመጫን የሚንቀሳቀሱትን ፀረ-ሰላም ሃይሎች አካሄድ በአግባቡ መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
የሰላም ስራዎች እንዳይሰሩ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሌት ተቀን የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸው ግልጽ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ኃይሎች ከተለያዩ አካላት ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ሀብት እየዘረፉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ዳግም ግጭት ለመቀስቀስና መንግስትን ለማፍረስ የሚፈልጉ አካላት በስፋት እየተስተዋሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ወጣት ፍላጎት ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ ህዝቡና የጸጥታ አካላት ብሎም ወጣቱ እነዚህ ኃይሎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እስካልተቀበለው ድረስ ለብቻቸው የሚያመጡት ለውጥ እንደማይኖርም ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡
አብዛኛው ህዝብ ለሰላም የሚሰራ ከሆነ የተወሰነ ቡድን ብቻ የአካባቢውን ሰላም ማደፍረስና ሀገር ማተራመስ የሚችልበት እድል እንደማይኖረውም ጠቁመዋል፡፡
ህዝቡ የጸረ ሰላም ኃይሎችን አካሄድ በመረዳቱና እነዚህን ኃይሎች ማስታገስ የሚያስችል አቅም ስላለው ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል እምነት የለኝም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ህዝባችን ከጉዳት ያልወጣና በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የህዝቡ ፍላጎት ከደረሰበት ጉዳት መውጣት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አጥፊ ኃይሎችን ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትግራይ ህዝብ ይህንን በተሟላ ሁኔታ እየገለጸ መሆኑንና የፌደራል መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥ እየጠየቀ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የክልሉ መንግስት ሁኔታዎችን ማረጋጋት እንዳለበት ጠቁመው፤ ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ የሆኑ አጀንዳዎች ከተፈጠሩ በጋራ መፍትሄ እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት፡፡
የትግራይ ህዝብ ለሰላም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ