Fana: At a Speed of Life!

ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ  አሁንም የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወሳኝ በሆኑ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ አሁንም ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በሴቶች ልማት ላይ በኒውዮርክ እየመከረ በሚገኘው 69ኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ያለው የኢትዮጵያ ልዑክ፤ ከጉባዔው ጎን ለጎን በዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና በኦስትሪያ መንግሥት የጋራ ትብብር በሴቶችና አረንጓዴ ፈጠራ ዙሪያ በተዘጋጀ ውይይት ላይ ተሳትፏል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በማንፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በኢነርጂ መስክ ትልቅ እርምጃ እየወሰደች እና የኢንዱስትሪ ሽግግርም ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ያሉ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የረጅም ጊዜ የልማት እቅዶች በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ አመቺ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ፈጠራን ማዕከል ያደረገ ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብ ሲያስቀምጥ፤ የስርዓተ ፆታ እና አካታችነት ጉዳይ ዋነኛ ምሰሶ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሴክተር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ያለ ሴቶች የተሟላ ተሳትፎ እውን ማድረግ አዳጋች እንደሆነም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ስራዎች አንስቶ በፈጠራ የታገዘ የግብርናና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ አላቸው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ወሳኝ በሆኑ ፈጠራና የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ አሁንም አናሳ ነው ብለዋል፡፡

ዘላቂነትን፣ ማኅበራዊ ተፅዕኖና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቅድሚያ ሰጥተው የተቋቋሙና በሴቶች የሚመሩ የንግድ ዘርፎችም ቢሆኑ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ውስንነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ከመጪው ጊዜ ጋር አብሮ የሚጓዝ ኢንዱስትሪ መገንባት የምንሻ ከሆነ፤ ሴቶች የኢንዱስትሪ ውጤቶች ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ግንባር ቀደም የፈጠራ ባለቤት፣ ውሳኔ ሰጪና የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎቻችን አካታችና ከስርዓተ ፆታ እኩልነት ግቦች ጋር በሚገባ ማስተሳሰር፣ ለሴት ስራ ፈጠሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ማበረታታት እንዲሁም በቴክኖሎጂ አመንጪ፣ አቅራቢና ተጠቃሚዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም መንግስት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የግሉ ሴክተር በቅንጅትና በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.