የመዲናዋ ነዋሪ የአካባቢ ብክለትን እንዲከላከል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነዋሪው በዋናነት ለራሱ ጤና ሲል የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቱን እንዲያስተካክል እና ብክለት እንዲከላከል የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ለሁለት ቀናት ከሁሉም የኮሪደር ልማት አስተባባሪዎች ጋር በመሆን በ2ኛው ምዕራፍ እየለሙ ያሉ ስምንት ኮሪደሮችን የሥራ አፈጻጸም ገምግመናል ብለዋል፡፡
የ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ፤ 135 ኪሎ ሜት ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታን ጨምሮ 42 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የወንዝ ዳርቻ ልማት እና 431 ሔክታር የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማችን ያለውን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማዘመን ከምንሠራው ሥራ በተጨማሪ፤ 23 ሺህ 320 በላይ መኪኖችን የማቆም ዐቅም ያለው የፓርኪንግና ተርሚናሎች ግንባታ፣ 112 የሕዝብ የመጸዳጃ ቦታዎች ግንባታ ተካትተዋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም የ2 ሺህ 669 ሕንጻዎች እድሳት፣ የሕጻናት መጫወቻ ሜዳዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የሕዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን ማካተቱን አንስተዋል፡፡
በዚህ ሥራም ከ62 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማውን በመበከል የሕዝቡን ጤና በመጉዳት ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩትን ሕግ እና ሥርዓት አውጥተን የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ እየተገበርን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የወንዞችን ብክለት በመከላከል በኩልም፤ ጽዱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ለመፍጠር የብክለት መከላከል ሕግ ሕብረተሰባችን መቀበሉን እና እየተገበረው መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡
በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልገነቡ እና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓታቸውን ያላስተካከሉትን በመቅጣት ላይ እንገኛለን ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ከቅጣቱ በላይ የምንፈልገው ሕዝባችን በዋናነት ለራሱ ጤና ሲል የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቱን እና ብክለት መከላከልን እንዲተገብር በመሆኑ፤ ሁላችንም ለዚህ ርብርብ እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ያቀረብንላቸውን ጥሪ በመቀበል ሕንጻዎችን በማደስ፣ ቀለም በመቀየር እና በከተማዋ ስታንዳርድ መሰረት መብራት በመዘርጋት እያገዙን የሚገኙ የከተማችን ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም የመንግሥትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ሙያዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ እያደረጉልን የሚገኙ ነዋሪዎቻችን እናመሠግናለን ብለዋል፡፡
በቀሪ ጊዜያት ልዩ ክትትል በማድረግ ቶሎ መጠናቀቅ ያለባቸውን ሥራዎች መጨረስ፣ መደገፍ የሚገባቸውን ደግሞ እየደገፍን ሕዝባችንን በታማኝነት ለማገልገል በገባነው ቃል መሰረት 2ኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አጠናቅቀን ለግልጋሎት ክፍት የምናደርግ ይሆናል ሲሉም አመላክተዋል፡፡