Fana: At a Speed of Life!

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ኤድዋርዶ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትን ጎብኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

በጉብኝታቸውም በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የሚገኙ ልዩ ልዩ ቅርሶችን መመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በብሔራዊ ቤተ-መንግሥቱ ውብ ገጽታ እና በውስጡ በሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች መደነቃቸውንም ገልጸዋል።

የኩባ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በበርካታ ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኩባ ታሪካዊ ወዳጅ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ሲመጡ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውንም አንስተዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ መስዋዕትነት ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ እና ረጅም ዘመናትን የተሻገረ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገውን የሀገራቱን ትብብር ወደ ላቀደ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ሣይንስ፣ ትምህርት እና በባህል ትልቅ ዐቅም እንዳላቸው ጠቁመው፤ በዘርፎቹ ያላቸውን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.