የትግራይ ክልል ለምርጫ የጀመረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም የፌዴሬሽን ም/ቤት አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የጀመረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
ምክር ቤቱ ለትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የሕገ መንግስት ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሷል፡፡
በዚህም የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ምርጫን በወቅቱ ለማካሄድ ከአቅም በላይ የሆነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ባለመደንገጉ እና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ክፍተቱን በህገ መንግስት ትርጉም መሙላት ተገቢ መሆኑን በማመን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑንም አስታውሷል፡፡
ይሁንና የትግራይ ክልል መንግስት ይህን ውሳኔ ወደጎን በመተው በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠናል ያለው ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ አንደቀጽ 102 መሰረት በፌዴራልና በክልል ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት ማካሄድ የሚችለው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነና በክልል ደረጃ የሚቋቋም ምርጫ ቦርድ አለመኖሩን ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት የወሰነው ውሳኔና የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት ያሳለፈውን ውሳኔ ያላከበረ ከመሆም ባሻገር ግልጽ የሆነ የህገ መንግስት ጥሰት ነው ብሏል ምክር ቤቱ በደብዳቤው፡፡
በተጨማሪም በሀገ መንግስቱ አንቀጽ 62 (9) መነሻ በማድረግ ማንኛውም ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስ ህገ መንግስዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12 መሰረት በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም እውቅና ህገ መንግስቱን ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ በግልጽ መደንገጉን ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን ለማካሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ ህገ መንገስቱን የሚቃረን፡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥልና የኢትዮጵያን የፌዴራል ስርዓት የሚጎዳ አካሄድ ነው ብሎታል፡፡
በተጨማሪም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 50 (8) መሰረት ለፌደራል መንግስት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር ያለበት መሆኑና የህገ መንግስት የበላይነት በሚደነግገው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) መሰረት፡ ማንኛውም ህግ ወይም የመንግስት አካል ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግስት ህገ መንግስቱንና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ እንዲያከብርና የጀመረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡