የዓድዋን ድል ስናስብ ለድል ያበቃንን የሀገር ፍቅር እና አንድነት የአሁኑ ትውልድ መጠበቅ አለበት – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋን ድል ስናስብ ለድል ያበቃንን የሀገር ፍቅር እና አንድነት የአሁኑ ትውልድ መጠበቅ አለበት ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ስነ ሥርዓቶች ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዓድዋ ድል አባቶቻችን ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጡትን ድል የነሱበት ጊዜ በመሆኑ ልንኮራ ይገባል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም የሚፈትኑ ችግሮችን በሙሉ አንድነት እና ህብረትን በማጠናከር ሊፈታ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሁኑ ጊዜ ውድድር በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ስለሆነ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን በመሥራት ታላቅ ሀገር በጋራ መገንባት አለብን ብለዋል።
ሀገራችን ለትውልድ የምትመች እንድትሆን በጋራ መስራት አለብን ሲሉም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
በደብሪቱ በዛብህ